2 ሲህሩ አል- ሀቂቃህ


ሺፋዕ የመንፈሳዊ ህክምና እና የምክር አገልግሎት
https://www.facebook.com/nosihr

2. ሲህሩ አል- ሀቂቃህ
  
ይህ ከድግምት ዓይነቶች አንዱ ነው ይኽውም በመድሃኒቶች በማነብነብና ሰይጣናዊ መልዕክቶችን በመፃፍ የሚሰራ ነው፡፡ በመቋጠር የሚሰራው ድግምት በልብ ላይ፣በሰውነት አካል ላይና በአእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡
  አቡ መሀመድ አል መቅዲሲ አልካፊ በተባለው መጽሀፋቸው እንዲህ ይላሉ  ድግምት ማለት በመድሃኒት፣ በማነብነብና በመቋጠር የሚሰራ ሲሆን በሰውነት ላይ እና በልብ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል ያሳምማል፣ ይገላል፣ በባልና ሚስት መሀከል ይለያያል፡፡ ከባል ወይም ከሚስት አንዳቸውን በመያዝ አንዳቸው ወደ አንዳቸው እንዳይቀርቡ ያደርጋል፡፡

አላህ  እንዲህ ብሏል፡-
فَيَتَعَلَّمُونَ مِنْهُمَا مَا يُفَرِّقُونَ بِهِ بَيْنَ الْمَرْءِ وَزَوْجِهِ  البقرة: ١٠٢ 

‹‹ከእነሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ፡፡›› (አል በቀራህ 1ዐ2)

‹‹በል «በተፈልቃቂው ጎህ ጌታ እጠበቃለሁ፡፡ ከፈጠረው ፍጡር ሁሉ ክፋት፡፡ ከሌሊትም ክፋት ባጨለመ ጊዜ፤ በተቋጠሩ (ክሮች) ላይ ተፊዎች ከኾኑት (ደጋሚ) ሴቶችም ክፋት፡፡›› (አል ፈለቅ 1-5)

     ይህ ማለት እነዚያ ሴት ደጋሚዎች በድግምታቸው ላይ ቋጠሮን የሚያስሩ ከዚያም በቋጠሩት ላይ የሚተፉ መሆናቸወን የተገለፀና እንዲሁም ድግምት ተፅእኖ የማያሳድር ቢሆን ኑሮ ከእርሱ በአላህ እንድንጠበቅ ባልታዘዝን ነበር፡፡ ደጋሚዎች ድግምትን መስራት ሲፈልጉ ክሮችን ይቋጥራሉ በእያንዳንዱ ቋጠሮ ላይ የሚፈልጉትን ነገር እስከሚደግሙ ድረስ ይተፉበታል፡፡ ስለዚህ አላህ  ከተንኮላቸው በእርሱ እንድንጠበቅ አዟል፡፡

“ሚን ሸሪ ነፋሳቲ ፊል ኡቀድ” ይህ ማለት እንዲህ አይነት ተግባር ከሚሰሩ ሴት ደጋሚዎች በአላህ መጠበቅ ነው፡፡ “አነፈስ” ማለት ከምራቅ ጋር የተቀላቀለ እስትንፋስ ሲሆን ከትፍታ ይለያል፡፡ እርሱ በስትንፋስና በመትፋት መሀከል ያለ ነው እንዲህ አይነት ትፍታ የደጋሚ ተግባር ነው፡፡

ነፍሱ መጥፎንና ተንኮልን በሚደገምበት ግለሰብ ላይ ለማሳረፍ ባሰበ ጊዜ በእርኩስ መንፈስ ይታገዝና በተቋጠረው ላይ ምራቅ የተቀላቀለበት እስትንፋስ ይነፋበታል፡፡ እርኩስ የሆነ እስትንፋስ ከሸርና ከመጥፎ ነገር ጋር ሆኖ ከምራቅ ጋር ተደባልቆ ይወጣል፡፡ በሚደገመው አካል ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድር እርኩስ መንፈሱ እገዛ ያደርግለታል፡፡ በአላህ ፍቃድ ድግምቱ ያገኘዋል፡፡
የደጋሚዎች ተንኮል!

ድግምት ለመስራት ደጋሚው ድግምት ከሚያደርግበት አካል የሆነ ነገር ይወሰዳል ወይም ከልብሱ ቁራጭ የሆነ ወይም ከእራሱ ፀጉር የተወሰነ አልያም ከጥፍሩ የተወሰነ እንዲመጣለት ያደርጋል፡፡ ይህ ሁሉ ካልተገኘ የእናቱን ስም ይጠይቃል ድግምቱን ከሚደገምበት ግለሰብ ጋር ለማያያዝ ከዚህ በኃላ የድግምቱ ተፅእኖ በውስጡ ይሆን ዘንድ ቋጠሮውን ይቋጥራል፡፡ ከዚያም ሰይጣናዊ መጠበቂያውንና ሰይጣናዊ መልዕክቱን ያነበንባል፡፡ ይህን የሚያደርገው ከእርኩስ መንፈሱ ድግምቱን ለማስፈፀም እገዛን ፈልጐ ሲሆን እነዚያ ከአላህ ውጪ የሚገዟቸውና የሚታዘዟቸው ሞገደኛ ሰይጣኖች ይረዱታል፡፡

እርኩስ መንፈሶች ድግምቱ ከሰውነቱ ጋር እንዲቆራኝ ያመቻቹለታል፡፡ ከዚያም ከእርሱ መለየት ፈፅሞ አይችልም፡፡ ይህ ሰይጣን ድግምት ከተሰራበት ግለሰብ ጋር የተቆራኘው የደጋሚው አገልጋይ በመባል ይጠራል፡፡ ዘውትር ከእርሱ ጋር ይሆናል የሆነ አጋጣሚ አግኝቶ ሰውነቱ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ይከታተለዋል፡፡ የዚህን ጊዜ ድግሞቱ ካልከሸፈና ቋጠሮው ካልተፈታ በስተቀር ከድግምቱ አይላቀቅም፡፡ ከዚያም የታሰረችዋ ቋጠሮ ከነጭ ወረቀቶች ጋር በውስጡ ሰይጣናዊ መልዕክት ባላቸው ነገራቶችና መጠበቂያዎች በቅርብ ቦታ አልያም ከተደገመበት ግለሰብ ራቅ ባለ ቦታ ድግምቱ ዘውትር እንዳይሆንበት ይቀመጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በመሬት ውስጥ ትቀበራለች ወይም ድብቅ በሆነ ቦታ ትቀመጣለች፡፡ ቦታዋ ታውቆ ድግምቱ ውድቅ እንዳይሆን ተብሎ፡፡

በተጨማሪም ፍትወት፣ የወርአበባ ደምን የመሰለ ከደረቀ በኃላ ይወቀጥና ይደባለቅበታል፡፡ እንደ “ፓውደር” ወይም ዱቄት ይሆንና በሱ ላይ ሰይጣናዊ መጠበቂያዎችን ያነቡበታል፡፡ ድግምት የተሰራበትን ንጥረ ነገር ድግምት ሊሰራበት ለታሰበበት ግለሰብ በምግብ ውስጥ ወይም በመጠጡ ውሰጥ ተደርጐበት በሆዱ ውስጥ ፀንቶ እንዲቀርና እርኩስ መንፈስን ወይም የደጋሚውን አገልጋይ ወደ ሰውነቱ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ እርኩስ መንፈስ በሰውነቱ ውስጥ ከሰፈረ ድግምት የተሰራበትን አላማ በማስፈፀም ላይ ይሰማራል፡፡

 አላማው በባልና በሚስት መሀከል መለያየት ከሆነ ባል በሚስቱ ላይ በሚጠላው ተግባር ወይም ሚስት በባሏ ላይ በምትጠላው ተግባር ላይ ይሰማራሉ፡፡ በሚስቱ አፍ ውስጥ ዘውትር የማይጠፋ መጥፎ ሽታ እንደመፍጠር የመሰለ ወይም ባል ከሚስቱ ጋር በቤት ውስጥ በሚሆንበት ወቅት ለባል አልያም ለሚስት ከፍተኛ ጥበትና መጨናነቅ እንዲሁም ፍራቻን ይፈጥሩባቸዋል፡፡ ቁጣው ይገነፍላል አንድ ንግግር እንኳን ከሚስቱ መሸከምን አይችልም ሌሎች ቤተሰብን ሊያፈርስ የሚችሉ ተግባሮች ይከሰታሉ፡፡

ደጋሚው ሰውየው ላይ ከደገመበት በኃላ ከድግምቱ የተፈለገው ድግምት የተደረገበትን ግለሰብ መጉዳት ከሆነ ሀይለኛ ህመም (ራስ ምታት) በራሱ ላይ፣  ሀይለኛ ህመም በወገቡና በመገጣጠሚያዎች ላይ፣  የልብ መጨናነቅና የሆድ ህመምን እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ፡፡

   ከድግምቱ የተፈለገው ድግምት የተደረገበትን ግለሰብ ከትምህርቱ ወይም ከንግዱ ወይም ከወደፊት ህልሙ ማደናቀፍ ከሆነ ሀሳቡን በመበታተንና እንቅልፍ እንዲያጣ በማድረግ፣ እረፍት በመንሳት፣ ቅዠትና ፍራቻን በእንቅልፍ ጊዜ በማምጣትና ሌሎችንም ደጋሚዎች የሚሰሩትን በመፈፀም ያከናውናል፡፡

  ይህ ሁሉ ጉዳት አላህ  እንዳለው በእርሱ ፍቃድ ብቻ ሲሆን ነው፡፡
وَمَا هُم بِضَارِّينَ بِهِ مِنْ أَحَدٍ إِلَّا بِإِذْنِ اللَّهِالبقرة: ١٠٢
‹‹እነርሱም በአላህ ፍቃድ ካልሆነ በእርሱ አንድንም ጐጂዎች አይደሉም››
 (አል በቀራህ 1ዐ2)

የአንድ ግለሰብን ጉዳት አላህ  የፈቀደ ከሆነ በዚህ ድግምት አማካኝነት ጉዳቱ በግለሰቡ ላይ ይከሰታል፡፡

 ይህ የድግምት አይነት (ሲህሩ አልጠላሲም) አደገኛ የድግምት አይነት ሲሆን አብዛኞቹ በዘመናችን ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ደካማ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸው ብዙዎቹ በዚህ ውስጥ ፍላጐታቸውን ለማሟላትና ብቀላቸውን ለመወጣት እንዲሁም እንደ እሳት የሚያቃጥላቸውን ምቀኝነታቸውን ከሰዎች ጠላት አድርገው በያዟቸው ግለሰቦች ላይ ማስፈፀም ችለዋል፡፡ በምድር ላይ ጥፋትን አስፋፉ፤ አላህ  ጥፋትን አይወድም፡፡

#ሺፋዕ

ፔጁን ላይክ ለማድረግ፡-

https://www.facebook.com/nosihr

ሼር በማድረግ ሙስሊሙን ዑማ በብዛት እየጎዳ ያለውን የሲህር በሽታ ለመከላከል የበኩሎን አስተዋፅዖ ያበርክቱ!
ፔጁን ላይክ ለማድረግ፡-


Comments